ከነቢዩ ሙሀመድ(ሰዐወ) መላክ በፊት የሴቶች መብት እና በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የነበራት ስፍራ በጣም የወረደ እና ይልቁንስ እንደማንኛውም የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መብቶች እንኳን የማይሰጣት ምስኪን ፍጥረት ነበረች። በተለይም በአረቡ አለም። ሴት በመሆኗ ብቻ የመኖር መብት የተነፈገችበት ጊዜ ነበር። አንድ አባት ሴት ልጅ ስትወለድ ሀፍረትና ውርደት ነበር የሚሰማው፤ እናም ከዚህ ውርደት ጋር መኖር እንደሌለበት በማሰብ የተወለደችለትን ልጅ አይኗ እያየ ከነሕይወቷ ከሚረማመድበት ምድር ስር ይከታታል።
በሌላ መልኩም ሴት ልጅን ሕይወት እንዳለው ፍጥረት ሳይሆን እንደ ዕቃ ነበር የሚመለከቷት፤ በጨዋታቸው ላይ እንደ ገንዘብ ሴት ልጅን ነበር አስይዘው ቁማር የሚጫወቱት። ከዚህ በበለጠ ደግሞ የሚገርመው ሴት ልጅ ሕይወት አላት ወይንስ የላትም የሚል ክርክር እና ውይይት የሚደረግባት ፍጥረት ሆና ቆይታ ነበር። ብቻ ብዙ ብዙ …
የነቢዩ ሙሀመድ(ሰዐወ) መላካቸው ግን እነዚህን ታሪኮች በሙሉ ቀያሪ ሆነ፤ የሴቶች ህይወት እንደገና አበበ። ሴት ልጅ እንደ ገንዘብ የምትወረስ ሳይሆን ወራሽነቷ ተረጋገጠ፣ ነገሩ ሴት ህይወት የላትም ሳይሆን የህብረተሰቡ ግማሽ አካል እንዲያውም ከዚያ በላይ መሆኗ ተረጋገጠ።
ነገር ግን ይህን እና ሌሎችን መብቶች በማስተባበል የእስልምናን እውነታ ባለማወቅም ሆነ እያወቁ እስልምና ሴት ልጅን እንደሚበድል በተለያዩ ሚዲያዎችና የሀይማኖት ተከታዮች ይለፈፋል። እስቲ እስልምና ወይንስ ክርስትና የሴትን ልጅ መብት የሚያረጋግጠው …
የሴቶች መብት እና ክብር በመፅሐፍ ቅዱስ(በጥቂቱ)
- ወደ ጢሞቲዎስ 2፡12 -14 ሴት ልጅ ወንድን ማስተማርም ሆነ በወንድ ላይ ምንም ስልጣን ሊኖራት አይችልም ይህ የሚሆነውም በመጀመሪያ የተፈጠረው አዳም በመሆኑ ነው።
- ወደ ቆሮንጦስ 11፡ 5 – 10 ሴት ልጅ ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም፤ ሴት ለወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት አልተፈጠረም።
- ኦሪት ዘዳግም 22፡28 ለሌላ የታጨችን ልጃገረድ ድንግልና የወሰደ ለአባቷ ሀምሳ ጥሬ ብር ዋጋ ይከፍላል እሷም ያለ ፍላጎቷ ሚስት ትሆናለች በሕይወት ዘመኑ ሁሉ መፍታት አይችልም
- መፅሐፈ መሳፍንት 21፡20 ሴት ልጅን መጥለፍ እንደሚፈቀድ ይናገራል
- ኦሪት ዘሌዋዊያን 12፡2-8 – ሴት ልጅ ወንድ ልጅ ከወለደች ለ 7 ቀን ትረክሳለች
– ሴት ልጅ ሴት ብትወልድ ለ 17 ቀን ትረክሳለች
በመርከሷም ምክኒያት የሚቃጠል መስዋዕት ሆኖ የሚቀርብ አንድ ጠቦትና ለሀጢያት ስርየት መስዋዕት የሚሆን ዕርግብ ወይንም ዋኖስ ለእግዚአብሔር ቤት ካህን መስጠት አለባት
ከነዚህ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በግልፅ የምንረዳው መፅሐፍ ቅዱስ (ክርስትና ለሴት ልጅ መብት የቆመ የሴት ተከራካሪ ሳይሆን ተፈጥሮአዊ መብቶቿን እንኳን እንዳልሆነ ነው።)
የሴቶች መብት እና ስፍራ በኢስላም
በኢስላማዊው የቤተሰብ መዋቅር ውስጥ ሚስት የቤቷ ንግስት ነች። ነቢዩ(ሰዐወ) እንዲህ ብለዋል «ሚስት በባሏ ቤት ጠባቂ ነች እናም በቤተሰቡ ባህሪና ጉዳዮች ላይ ተጠያቂ ነች» ቡኻሪ የዘገቡት
– ሴት ልጅ ከቤት ውጪ በሚከናወኑ ሃይማኖታዊ ግዴታዎች ነፃ ነች ቡኻሪ የዘገቡት
– ሴት ልጅ ረጅም ጉዞ ለማድረግ ብትፈልግ ምንም አይነት ጥቃት እንዳይደርስባት ከቅርብ ቤተሰቧ ጋር (አባት፣ ወንድም፣ ባለቤት፣ አጎት፣ ልጅ) መሄድ ግዴታነቱን ኢስላም ደንግጓል።
– ሴት ልጅ ያለምንም በቂ ምክኒያት ከቤት መውጣቷን ኢስላም አያበረታታም
– ሴት ልጅ የትዳር አጋሯን የመምረጥ መብት አላት
– ነቢዩ(ሰዐወ) እንዲህ ብለዋል «አንዲት ሴት(አግብታ የምታውቅ) ከቤተሰቧ ይልቅ የራሷን እጣ የመወሰን መብት አላት አግብታ የማታውቅን ሴት ያለ ፍቃድ አታኑሯት»
– ባሎቻቸው የሞቱባቸው የተፈቱ ሴቶች እና ጋብቻቸው በህግ ውድቅ የተደረገ ሴቶች አዲስ ትዳር የመመስረት ሙሉ በሙሉ መብት አላቸው።
«ለእነርሱም (ለሴቶች) የዚያ በእነርሱ ላይ ያለባቸው (ግዳጅ) ብጤ በመልካም አኑዋኑዋር (በባሎቻቸው ላይ መብት) አላቸው፡፡» ሱረቱ አል በቀራህ 228
– ሴት ልጅ የመውረስ መብት አላት
«ለወንዶች ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተዉት (ንብረት) ፋንታ (ድርሻ) አላቸው፡፡ ለሴቶችም ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተዉት ከእርሱ ካነሰው ወይም ከበዛው ፋንታ አላቸው፡፡ የተወሰነ ድርሻ (ተደርጓል)፡፡» ሱረቱ አን ኒሳእ 7
– ሴት ልጅ በሰብአዊነቷ ከወንድ እኩል ነች፤ ወንድም ሆነ ሴት ምንዳቸውን የሚያገኙት በሰሩት ስራ ልክ ነው።
«አላህም ከፊላችሁን በከፊሉ ላይ በእርሱ ያበለጠበትን ጸጋ አትመኙ፡፡ ለወንዶች ከሠሩት ሥራ እድል አላቸው፡፡ ለሴቶችም ከሠሩት ሥራ ዕድል አላቸው፡፡ አላህንም ከችሮታው ለምኑት፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡» ሱረቱ አን ኒሳእ 32
«ሙስሊሞች ወንዶችና ሙስሊሞች ሴቶች፣ ምእምናንና ምእምናትም፣ ታዛዦች ወንዶችና ታዛዦች ሴቶችም፣ እውነተኞች ወንዶችና እውነተኞች ሴቶችም፣ ታጋሾች ወንዶችና ታጋሾች ሴቶችም፣ አላህን ፈሪዎች ወንዶችና አላህን ፈሪዎች ሴቶችም፣ መጽዋቾች ወንዶችና መጽዋቾች ሴቶችም፣ ጿሚዎች ወንዶችና ጿሚዎች ሴቶችም፣ (ካልተፈቀደ ሥራ) ብልቶቻቸውን ጠባቂዎች ወንዶችና ጠባቂ ሴቶችም፣ አላህን በብዙ አውሺዎች ወንዶችና አውሺዎች ሴቶችም፣ አላህ ለእነርሱ ምሕረትንና ታላቅን ምንዳ አዘጋጅቶላቸዋል፡፡» ሱረቱ አል-አሕዛብ 35
ሴት ልጅ ታላቅ ስጦታ ናት
- «አካለ መጠን ደርሰው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ሁለት ሴት ልጆችን ያሳደገ የፍርዱ ቀን ከኔ ጋር እኩል ይቆማል» ብለዋል ሁለት ጣቶቻቸውን አጠጋግተው በማሳየት
- ሴት ልጆች ብቻ ያሉት ሰው እርሱም በትክክል ካሳደጋቸው ከጀሃነም እሳት ሽፋን ይሆኑለታል።
- ከመልካም ሚስት የበለጠ ፀጋ በዚህ አለም አይገኝም (ኢብን ማጃህ)
- አንድ ሰው ወደ ነቢዩ መጥቶ እንዲህ በማለት ጠየቀ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ይበልጥ እንክብካቤ ላደርግለት የሚገባኝ ሰው ማን ነው?» «እናትህ» አሉት «ከዚያስ» «እናትህ» አሉት «ከዚያስ» «እናትህ» አሉት «ከዚያስ» «አባትህ» አሉት። ወደ እናታችን በሶስት እጥፍ ስንቀርብ ወደ አባታችንአንድ ጊዜ ይሆናል ማለት ነው። ይህም እናት የወርቅ፣ የብር እና የነሀስ ድርሻ ሲኖራት አባት የሰርተፊኬት ድርሻ ያገኛል ማለት ነው።
የሴቶችን መብትና ክብር በእስልምና በዚህች ፅሁፍ የምናጠቃልለው አይደለም። ከባህር የማንኪያ ያህል ነው። ከዚህ ጋር መረዳት ያለብን ነገር ከማንም እና ከምንም የበለጠ ለሴት ልጅ ክብርና መብት ተቆርቋሪ ከእስልምና ውጪ አልነበረም፤ የለም፤ አይኖርምም። በአለማዊ ጥቅማጥቅሞች እና በምዕራባዊያን propaganda በሚዲያን መሰረተ ቢስ አስተምህሮቶች ይህን የማንነት መገለጫ፤ የሕይወቷ መሰረት ፤ የስኬታማነቷ መንገድ የሆነውን ሃይማኖት ልትለቅ አይገባም!!!!!!!!!!!!!!!