መቻልና ቁጣን መቆጣጠር (ክፍል 2)
ተግባራዊ ናሙናዎች
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ለራሳቸው ጉዳይ ተቆጥተው እንደማያውቁ ተነግሯል፡፡ የአላህ ወሰን ካልተደፈረ በቀር፡፡ “ጣኦታውያንን ይርገሟቸው” ተብለው ተጠየቁ፡፡ “አዛኝ እንጅ ተራጋሚ ተደርጌ አልተላክኩም፡፡” ሲሉ መለሱ፡፡ (ሙስሊም)
አቻ
ከማይገኝላቸው የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የይቅርታ ታሪኮች መካከል ለሙናፊቆች መሪ ለአብደላህ ቢን ኡበይ
ያደረጉት ይቅርታ ይጠቀሳል፡፡ አብደላህ የሙሰሊሞች ቀንደኛ ጠላት ነበር፡፡ ሁሌም ይተናኮላቸዋል፡፡ አጋጣሚ እየፈለገ
ያጠቃቸዋል፡፡
እነርሱን ለመጉዳት ከሰይጣናት ጋር ተባብሮ ይሰራል፡፡ እነርሱን ወይም ነቢዩን የሚያጠቃበት እድል ካገኘ እንዲሁ
አያሳልፈውም፡፡ በአኢሻ ላይ አግባብ ያልሆነ ወሬ ያስወራው እርሱ ነው፡፡ እኩያንም የርሱን ሐሰት ተቀብለው
በማሰራጨት የሕብረተሰቡን መሰረት እስከማናጋት ደረሱ፡፡ ግና አላህ እውነትን ይፋ አደረገ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን
አብደላህ ቢን ኡበይ በሞተ ጊዜ ልጁ መጥቶ ይቅር እንዲሉት ሲጠይቃቸው አላንገራገሩም፡፡ በቀሚሳቸው ይገነዝ ዘንድም
ጠየቃቸው፡፡ ቀሚሳቸውን ሰጡት፣ እንዲሰግዱበትና ምህረት ከአላህ እንዲለምኑለትም ጠየቃቸወ፡፡ ይቅር ባዩ ነብይ ይህን
ጥያቄውም እምቢ አላሉትም፡፡ ትላንት ክብራቸውን ካጎደፈው ሰው ጀናዛ ፊት ቆመው ምህረት ሊለምኑለት ሲሰናዱ አላህ
እንዲህ የሚል ትእዛዝ አወረደላቸው፡-
اسْتَغْفِرْ لَهُمْ أَوْ لَا تَسْتَغْفِرْ لَهُمْ إِن تَسْتَغْفِرْ لَهُمْ سَبْعِينَ مَرَّةً فَلَن يَغْفِرَ اللَّهُ لَهُمْ ۚ ذَٰلِكَ بِأَنَّهُمْ كَفَرُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ ۗ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الْفَاسِقِينَ
“ለእነርሱ
ምሕረትን ለምንላቸው፤ ወይም ለእነሱ ምሕረትን አትለምንላቸው (እኩል ነው)፡፡ ለእነሱ ሰባ ጊዜ ምሕረትን
ብትለምንላቸው አላህ ለነሱ በፍጹም አይምርም፡፡ ይህ እነርሱ አላህና መልክተኛውን በመካዳቸው ነው፡፡ አላህም
አመጸኞች ሕዝቦችን አያቀናም፡፡” (አልተውባህ 80)
አቡበክር አገልጋያቸውን ሲራገሙ የሰሙት ነብይ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ድርጊቱን ነቀፉ፡፡ እንዲህም አሉ፡-
“እውነት ባዩ ሲዲቅ ተራጋሚ ሊሆን አይገባም፡፡” (ሙስሊም)
በሌላ ዘገባ እንዲህ ማለታቸው ተወስቷል፡-
“ተራጋሚም ሲዲቅም ልትሆኑ አትችሉም፡፡”
አቡበክር ለዚህ ስህተታቸው ማካካሻ ይሆን ዘንድ አገልጋያቸውን ነጻ ለቀቁት፡፡ ከነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ዘንድ በመምጣትም፡- “ይህን ጥፋት ዳግም አልፈጽምም” ሲሉ ቃል ገቡ፡፡
በአኢሻ ላይ በተሰነዘረው የሐሰት ወሬ ስርጭት የተሳተፈውን ሙጦህ የተባለ ወዳጃቸውን እንደወትሮው ቀለብ ላይሰፍሩለት በማሉ ጊዜ አላህ የሚከተለውን መልእክት አወረደ፡-
وَلَا
يَأْتَلِ أُولُو الْفَضْلِ مِنكُمْ وَالسَّعَةِ أَن يُؤْتُوا أُولِي
الْقُرْبَىٰ وَالْمَسَاكِينَ وَالْمُهَاجِرِينَ فِي سَبِيلِ اللَّهِ ۖ وَلْيَعْفُوا وَلْيَصْفَحُوا ۗ أَلَا تُحِبُّونَ أَن يَغْفِرَ اللَّهُ لَكُمْ ۗ وَاللَّهُ غَفُورٌ رَّحِيمٌ
“ከእናንተም
የችሮታና የክብረት ባለቤቶች የኾኑት ለቅርብ ዘመዶችና ለድኾች በአላህም መንገድ ለተሰደዱ ሰዎች ላይሰጡ አይማሉ፡፡
ይቅርታም ያድርጉ፡፡ (ጥፋተኞቹን) ይለፉም፡፡ አላህ ለእናንተ ሊምር አትወዱምን᐀ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” (አል ኑር 22)
አቡበክርም፡- “አዎ፣ በአላህ እምላለሁ፣ አላህ እንዲምረኝ እፈልጋለሁ” አሉና ቀለብ መስፈራቸውን ቀጠሉ፡፡ “መቼም ቢሆን አላቆምበትም” ሲሉም ቃል ገቡ፡፡
ኢብን
አባስ እንዳስተላለፉት ኡየይናህ ቢን ሔስን በመጣ ጊዜ ከወንድሙ ልጅ ከጀድ ቢን ቀይስ ዘንድ አረፈ፡፡ ዑመር
ከሚያቀርቧቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ ጀድ የቁርአን አዋቂና የዑመር ምክክር (ሹራ) ጉባኤ አባል ነው፡፡
ዑየይናህም፡- “ወደ ዑመር እገባ ዘንድ አስፈቅድልኝ” አለው፡፡ አስፈቀደለትና ሲገባ “ዑመር ሆይ፣ እንደሚገባው
አትሰጠንም፡፡ በፍትህም አትፈርድልንም” አላቸው፡፡ ዑመርም በጣም ተቆጡ፡፡ ሊቀጡትም አሰቡ፡፡ እሱም፡- “የአማኞች
መሪ ሆይ፣ አላህ ለነቢዩ እንዲህ ብሏቸዋል፡-
خُذِ الْعَفْوَ وَأْمُرْ بِالْعُرْفِ وَأَعْرِضْ عَنِ الْجَاهِلِينَ
“ገርን ጠባይ ያዝ፡፡ በመልካምም እዘዝ፡፡ ባለጌዎቹንም ተዋቸው፡፡” (አል አእራፍ 199)
ይህ ሰው ከመሐይማን መካከል አንዱ ነው፡፡” አላቸው፡፡ ዑመር ይህን አንቀጽ ሊተላለፉ አልፈቀዱም፡፡ የአላህን ኪታብ መልእክት በወጉ የሚተገብሩ ሰው ነበሩ፡፡
ዑመር
የተቆጡት ይህ በደዊን ወሰን በማለፉ ነው፡፡ ሊቀጡት አሰቡም፡፡ ምክንያቱም የገባው ሊመክራቸው ወይም መብቱን ፈልጎ
ሳይሆን በሐላፊነት ላይ ያለን ባለስልጣን ያለ ምክንያት ለመስደብ ነው፡፡ ሰውየው ከመሐይማን መሆኑ ሲነገራቸው
ትተውት ዘወር አሉ፡፡
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ለአሸጅ አብዱልቀይስ እንዲህ ብለውታል፡-
“አላህ የሚወዳቸው ሁለት ባህሪያት አሉህ፡፡ እነርሱም ታጋሽነትና እርጋታ ናቸው፡፡” (ሙስሊም)
ኢማም ነወዊ ይህን ሐዲስ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፡-
“መታገስ
ማስተዋል ነው፡፡ እርጋታ ደግሞ ማረጋገጥና አለመቸኮል ነው' ነቢዩ ይህን ያሉበት አጋጣሚ አንድልዑክ መዲና
እንደደረሰ ወደ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ተጣድፎ ሄደ፡፡ አሸጅ ደግሞ ከማረፊያ ቦታቸውቆየ፡፡ ጓዙን
አስተካከለ፡፡ ግመሉን አሰረ፡፡ ጥሩ ልብስም ለበሰ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አመራ፡፡
ነቢዩ አቀረቡት፡፡ ከጎናቸውም አስቀመጡት፡፡
“ራሳችሁንና ወገኖቻችሁን ወክላችሁ ቃል ኪዳን (በይዓ) ትገባላችሁን?” ሲሉም ጠየቋቸው፡፡ ሰዎችም፡- “አዎ” አሉ፡፡ አሸጅ ግን እንዲህ አለ፡-
“የአላህ
መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሆይ፣ ራሳችንን ወክለን ከርስዎ ጋር ቃል እንጋባለን' ለወገኖቻችንም ጥሪ
የሚያደርግላቸው እንልካለን፡፡ የተከተሉን የኛው አካል ይሆናሉ፡፡ እንቢ ያሉንን ግን እንዋጋለን፡፡ ነቢዩም፡- “እውነት ብለሐል፡፡ አላህ የሚወዳቸው ሁለት ባህሪያት አሉህ'” በማለት ተናገሩ።
ቃዲ ኢያድ እንዳሉት እርጋታ የአንዳች እርምጃ ፋይዳ እስኪረጋገጥ ድረስ አለመቸኮል ነው፡፡ ታጋሽነት ደግሞ የአእምሮን ጤንነት፣ ብስለትና ፍጻሜን የማስተዋል ክሕሎቱን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የታጋሽነትና ቁጣን የመቆጣጠር መገለጫዎች
- የባለጌዎችን ሁከት ሳይበቀሉ መታገስ
- የተቃራኒ ወገንን እይታ ማክበር
- ከተቃራኒ ወገን እይታ አወንታዊ ገጽታውን ማየትና በርሱ ለመጠቀም መሞከር
- ክርክርንና ንትርክን መቀነስ
- ፍቅንና አክብሮትን ለማግኘት መትጋት
- ስህተትን መቀበል
- ከተረገመው ሰይጣን በአላህ ተጠበቅ
- ቆመህ ከሆነ ተቀመጥ፣ ተቀምጠህ ከሆነ ተጋደም
- ቁጣህ ካልበረደ ቦታውን ለቀህ ሂድ
- ውዱእ አድርግ
- ሁለት ረከዓ ስገድ፡፡ ሱጁድ አስረዝም፡፡
- ከነቢዩ የተገኘውን ተከታዩን ዱዓ አብዛ፡- “የነቢዩ ሙሐመድ ጌታ ሆይ፣ ወንጀሌን ማርልኝ፡፡ የቀልቤን ቁጣ አስወግድልኝ፡፡ መንገድ ከሚያስቱ ፈተናዎችም ጠብቀኝ፡፡”