ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) በኛ ላይ ያላቸውን ሃቅ እንዴት መጠበቅ እንችላለን?
አንድ ሙእሚን ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) በተመለከተ ሊተገብረው የሚገቡ ነገሮች እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡-
1. ንግርናቸውን እውነት ብሎ መቀበል
ማንኛውም
ሙእሚን ንግግራቸውን እውነት ብሎ ሊቀበል ይገባዋል። ምክንያቱም ከአላህ(ሰ.ወ) እንደተላኩ ያውቃል፣ ከራሳቸው
(ከልብ ወለድ) አንዳችም ነገር አይናገሩም አላህ (ሱ.ወ) ወህይ ያደረገላቸው ቢሆን እንጂ። አላህም ለዚህ አባባል
ምስክርነት ሰጥቷል፡-
وَمَا يَنطِقُ عَنِ الْهَوَىٰ ﴿ ٣﴾ إِنْ هُوَ إِلَّا وَحْيٌ يُوحَىٰ ﴿النجم: ٤﴾
ከልብ ወለድም አይናገርም። እርሱ (ንግግሩ) የሚወርረድ ራእይ እንጅ ሌላ አይደለም። (አል ነጅም 3-4)
2. ትእዛዛቸውን ማከበር
ጌታችን አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል
وَإِن تُطِيعُوهُ تَهْتَدُوا وَمَا عَلَى الرَّسُولِ إِلَّا الْبَلَاغُ الْمُبِينُ
ብትታዘዙትም ትምመራላችሁ። በመልእክተኛውም ላይ ግልጽ ማድረስ እንጂ ሌላ የለበትም» በላቸው። (አል ኑር 54)
አላህ (ሱ.ወ) የሱን ትእዛዝ ማክበር እሳቸውን ከመታዘዝ ጋር አቆራኝቶታል። ይህ ደግሞ ጌታችን ምን ያህል እሳቸውን እንዳላቃቸው ማሳያ ነው። አላህ (ሱ.ወ) በሱረቱ ኒሳእ እንዲህ ይለናል፡-
مَّن يُطِعِ الرَّسُولَ فَقَدْ أَطَاعَ اللَّهَ وَمَن تَوَلَّىٰ فَمَا أَرْسَلْنَاكَ عَلَيْهِمْ حَفِيظًا
መልክተኛውን የሚታዘዝ ሰው በእርግጥ አላህን ታዘዘ። ከትእዛዝም የሸሸ ሰው (አያሳስብህ)። በእነሱ ላይ ጠባቂ አድርገን አልላክንህምና። (አል ኒሳእ 80)
በተቃራኒው ደግሞ እሳቸውን ከመታዘዝ የታቀቡትን እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃቸዋል፡-
فَلْيَحْذَرِ الَّذِينَ يُخَالِفُونَ عَنْ أَمْرِهِ أَن تُصِيبَهُمْ فِتْنَةٌ أَوْ يُصِيبَهُمْ عَذَابٌ أَلِيمٌ ﴿النور: ٦٣﴾
እነዚያም ትዕዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ። (አል ኑር 63)
3. እሳቸውን መውደድ
ውዱ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይሉናል፡-
"لا يؤمن أحدكم حتى أكون أحب إليه من ولده ووالده والناس أجمعين" متفق عليه
“አንዳችሁ አላመነም እኔ እሱ ዘንድ ከልጆቹ፣ ከወላጆቹ እንዲሁም ከሰው ልጆች ሁሉ ይበልጥ ተወዳጅ እስከምሆን ድረስ። ” ( ቡኻሪና ሙስሊም)
አነስ (ረ.ዐ) ይህንን ይነግሩናል፡-
وعن
أنس رضى الله عنه أن رجلاً سأل رسول الله: متى الساعة؟ قال : وما أعددت
لها ؟؟ قال : لا شىء إلا أني أحب الله ورسوله، فقال أنت مع من أحببت. قال
أنس: فما فرحنا بشىء فرحنا بقول النبي"أنت مع من أحببت". قال أنس: "فأنا
أحب النبي وأبا بكر وعمر –رضى الله عنهما- وأرجو أن أكون معهم بحبي
إياهم."متفق عليه
“አንድ
ሰው ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ይመጣና ‘ቂያማ(እለተ ትንሳኤ) መቼ ነው?’ ብሎ ይጠይቃቸዋል። እሳቸውም
‘ለሷ ምን አዘጋጅተሃል?’ በማለት ይጠይቁታል። እሱም ‘በርግጥ ምንም አላዘጋጀሁም ነገር ግን አላህንና
መልእክተኛውን እወዳለሁ’ አላቸው። ‘አንተ ከወደድከው ጋር ነህ’ አሉት። ” አነስ (ረ.ዐ) ትረካውን በመቀጠል
“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ‘አንተ ከወደድከው ጋር ነህ’ የምትለውን ቃል ሲናገሩ የተደሰትነውን ያህል
በህይወታችን ተደስተን አናውቅም። ” በመቀጠልም “እኔ ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) እንዲሁም አቡበከርና ዑመርን (ረ.ዐ)
እወዳለሁ:: አላህን የምለምነው ለነሱ ባለኝ ፍቅር ነገ ከነሱ ጋር እንዲያደርገኝ ነው። ” (ቡኻሪና ሙስሊም)
4. አርዓያነታቸውን መከተል
ማንኛውም ሙስሊም የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ባህሪ መላበስ፣ ስነ- ምግባራቸውን መውረስ እንዲሁም ተምሳሌትነታቸውንም መከተል አለበት። አላህም (ሱ.ወ) እንዲህ ይለናል:-
لَّقَدْ
كَانَ لَكُمْ فِي رَسُولِ اللَّهِ أُسْوَةٌ حَسَنَةٌ لِّمَن كَانَ يَرْجُو
اللَّهَ وَالْيَوْمَ الْآخِرَ وَذَكَرَ اللَّهَ كَثِيرًا
ለእናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለሆነ ሰው፣ አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል አልላችሁ። (አህዛብ 21)
5. ሰለዋትን ማውረድ
ሙስሊም የሆነ ሰው በነብዩ ላይ ሰለዋት(የአክብሮት እዝነት) ማውረድን ማብዛት ይጠበቅበታል። በተለይ ስማቸው በሚወሳበት ጊዜ። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይለናል፡-
إنَّ اللَّهَ وَمَلَائِكَتَهُ يُصَلُّونَ عَلَى النَّبِيِّ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا صَلُّوا عَلَيْهِ وَسَلِّمُوا تَسْلِيمًا ﴿الأحزاب: ٥٦﴾
አላህና መላእክቱ በነቢዩ ላይ የአክብሮት እዝነትን ያወርዳሉ። እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በእርሱ ላይ የአክብሮት እዝነትን አውርዱ። የማክበርንም ሰላምታ ሰላም በሉ። (አል አህዛብ 56)
የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) ይህን የሚያበረታቱ ሃዲሶችን ነግረውናል፡-
"من صلى علىّ واحدة صلى الله عليه عشرًا" رواه مسلم
“እኔ ላይ አንድ ሰለዋት ያወረደ አላህ በሱ ላይ በአስር እጥፍ ያወርድበታል” (ሙስሊም)
በሌላ ሃዲሳቸውም:-
"البخيل من ذكرت عنده، فلم يصل على" رواه الترمذى وأحمد والنسائي
“ስስታም ብሎ ማለት እሱ ዘንድ ስሜ ተወስቶ ሰለዋት የማያወርድ ነው። ” (ቲርሚዚ፣ አህመድ፣ ነሳኢይ)
ለአንድ
ሙስሊም ሃሙስ ሌሊትና ጁመዓ ቀን እንዲሁም ከሁሉም አዛኖች ማበቂያ በኋላና በመጨረሻው ተሸሁድ ወቅት በተጨማሪም
ስማቸው ሲወሳ ባጠቃላይ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰለዋት ማውረዱ በጣም ተወዳጅና አስፈላጊ ተግባር ነው። በተለያዩ
መንገዶች ሰለዋት ማውረድ ብንችልም የተሟላው ሰለዋት ደግሞ የሚከተለው ነው።
"اللهم
صل على محمد وعلى آل محمد، كما صليت على إبراهيم وعلى آل إبراهيم، وبارك
على محمد وعلى آل محمد، كما باركت على إبراهيم وعلى آل إبراهيم، إنك حميد
مجيد"
“አላህ ሆይ በሙሀመድ ላይና በሙሀመድ በቤተሰቦች ላይ እዝነትህን አስፍን። ልክ በኢብራሂም እና በቤተሰቦቹ ላይ እንዳሰፈንከው ሁሉ። በረከትህንም በሙሀመድና በቤተሰቦቻቸው ላይ አስፍን። ልክ በኢብራሂምና በቤተሰቦቹ ላይ በረከትህን እንዳሰፈንከው ሁሉ። አንተ ምስጉንና የላቅክ ነህና። ”( አህመድ)
6. ለሳቸው ዱዓ ማድረግ
የአላህ መልእክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይሉናል፡-
"إذا سمعتم المؤذن فقولوا مثل ما يقول، ثم صلوا علىّ؛ فإنه من صلى علىّ صلاة صلى الله عليه بها عشرًا،
ثم سلوا لي الوسيلة، فإنها منزلة في الجنة، لا تنبغي إلا لعبد من عباد
الله، وأرجو أن أكون أنا هو، فمن سأل لي الوسيلة حلت عليه الشفاعة" رواه
مسلم
“ሙአዚን
(አዛን) ሲል ስትሰሙ እሱ የሚለውን ተከትላችሁ በሉ። ከዚያም በኔ ላይ ሰለዋትን አውርዱ። በኔ ላይ አንድን
ሰለዋት ያወረደ አላህ በሱ ላይ በአስር እጥፍ ያወርድበታልና። ከዚያም ወሲላን ጠይቁልኝ። ይህች ወሲለ በጀነት ውስጥ
የምትገኝ ቦታ ናት። ይህች ቦታ ከአላህ ባሮች አንዱ እንጂ አይገባትም። ያ ባርያ እኔ መሆንን እከጅላለሁ። ለኔ
ወሲላን የጠየቀልኝ ሰው ምልጃዬ በቃችለት። ” (ሙስሊም)
በሌላ ሀዲሳቸውም፡-
"من
قال حين يسمع النداء : اللهم رب هذه الدعوة التامة، والصلاة القائمة، آت
محمدًا الوسيلة والفضيلة، وابعثه مقامًا محمودًا الذي وعدته، حلت له شفاعتي
يوم القيامة" رواه البخاري وأبو داود والترمذى .
“አዛን
በሚባልበት ወቅት “አላህ ሆይ! የዚህች ሙሉ ጥሪና የዚህች ለመሰገድ የተቃረበች ሰላትአምላክ ነህ:: ሙሀመድን
ወሲላና ፈዲላ የተባሉትን (የክብር ደረጃዎች) ለግሳቸው። ቃል የገባህላቸውን የተመሰገነ ደረጃም አጎናጽፈህ (ከሞት)
ቀስቀሳቸው።” የሚለውን ዱዓ ያደረገ የቂያማ እለት ምልጃዬ ተረጋገጠችለት። ” (ቡኻሪ፣ አቡዳውድ፣ ቲርሚዚ)
7. ሱናቸውን ህያው ማድረግ
ሱና
ስንል ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የተገኘ ንግግራቸው ወይም ተግባራቸው ማለት ነው። ማንኛውም ሙስሊም የሳቸውን
ሱና ህያው ለማድረግና ለመተግበር ጉጉ ሊሆን ይገባል። በተለይ በሰዎች ዘንድ የተዘነጋና የተተወን ሱና መስራት
ተወዳጅ ተግባር ነው። የአላህም መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በሃዲሳቸው እንዲህ ብለውናል፡-
"من أحيا سنة من سنتي فعمل بها الناس ، كان له مثل أجر من عمل بها لا ينقص من أجورهم شىء" رواه ابن ماجة
“አንዲት የተረሳች ሱናዬን ህያው ያደረገ ሰው ያቺን ሱና ሰዎች የተገበሯት እንደሆነ ለዚህ ሰው ሱናውን የሰሩት ሰዎች አጅር (ምንዳ) ከነሱ ሳይቀነስ ይደርሰዋል። ” (ኢብኑ ማጃህ)
በሌላም ሃዲሳቸው፡-
"..
فإنه من يعش منكم بعدي فسيرى اختلافًا كثيرًا، فعليكم بسنتي وسنة الخلفاء
المهديين الراشدين تمسكوا بها، وعضوا عليها بالنواجذ، وإياكم ومحدثات
الأمور؛ فإن كل محدثة بدعة، وكل بدعة ضلالة" رواه أحمد وأبوداود والترمذى
وابن ماجة
“እነሆ
ከኔ በኋላ የሚቆይ ሰው ብዙ ልዩነቶችን ያያል። በሱናዬና በቅን መሪዎች (ኹለፋኡ ራሺዲን) ሱና አደራችሁን ።
አጥብቃቸሁ ያዙ፣ በክራንቻ (ቅንጣጤ) ጥርሳችሁ ያዙ። አደራቸሁን አዳዲስ ነገሮችን ተጠንቀቁ። ምክንያቱም አዳዲስ
መጤ ነገሮች ሁሉ ፈጠራዎች ናቸው። ፈጠራዎች ሁሉ ደግሞ ጥመት ናቸው። ” (አህመድ፣ አቡዳውድ፣ ቲርሚዚ፣ ኢብኑ
ማጃህ)
8. ባልደረቦቻቸውን (ሰሃቦችን) መውደድ
ሙስሊም የሆነ ሰው ሰሃቦችን መውደድና ማክበር ይኖርበታል። የአላህ መልእክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ይመክሩናል፡-
"الله
الله في أصحابي ، الله الله في أصحابي ، لا تتخذوهم غرضًا بعدي ، فمن
أحبهم فبحبي أحبهم ، ومن أبغضهم فببغضي أبغضهم ، ومن آذاهم فقد آذاني ، ومن
آذاني فقد آذى الله ، ومن آذى الله فيوشك أن يأخذه " رواه الترمذى
“የሰሃቦቼን ነገር አደራችሁን፣ የሰሃቦቼን ነገር አደራችሁን ። ከኔ በኋላ (የነገር)ኢላማ አድርጋችሁ አትያዟቸው። እነሱን
የወደዳቸው በውዴታዬ ነው የወደዳቸው። እነሱን የጠላቸው ደግሞ እኔን ስለሚጠላ ይጠላቸዋል። እነሱን ያስቸገረ እኔን
አስቸገረ፤ እኔን ያስቸገረ በርግጥ አላህን አስቸገረ፤ አላህን ያስቸገረ በርግጥ አላህ ሊይዘው ይቀርባል።
”(ቲርሚዚ)
ሰሃቦችን
ከመውደድ መገለጫዎች መካከል ስማቸው በሚነሳበት ጊዜ “ረዲየላሁ ዐንሁም” (አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸው)
ማለት ዋነኛው ነው። ሌላው በሰሃቦች መካከል በተነሳ ልዩነትና አለመስማማት ውስጥ ጠልቆ በመግባት የሆነ ያልሆነውን
ከመዘባረቅ መቆጠብ ነው። እንዲሁም ለነሱ ዱዓ ማድረግ፣ የነሱን ክብር የሚነካ ነገር ከተሰራ መከላከል በዋነኛነት
የሚጠቀሱ ናቸው።
9. ሲራን (የህይወት ታሪካቸውን) ጠንቅቆ ማወቅ
አንድ ሙስሊም የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ታሪክ በደንብ ጠንቅቆ ማወቅ ይገባዋል። ይህም እለት ተእለት እንቅስቃሴው ውስጥ የህይወት ምሳሌያዎቻቸውን በአርአያነት እንዲጠቀም ይረዳዋል።
10. ንግግሮቻቸውን በጥንቃቄ መሰብሰብና ለሰዎች ማድረስ
ማንኛውም
ሙስሊም አንድን የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ንግግር በሃዲስነት ሲያስተላልፍ ትክክለኛ (ሰሂህ) መሆኑን ከማስተላለፉ በፊት
ማረጋገጥ ይኖርበታል። የሚያስተላልፈው ሃዲስ ደካማ (ደዒፍ) የሆነ እንደሆነ ይህንን በግልፅ ለሰዎች ሊያሳውቅ
ይገባል። የተጣሉ የሆኑ ወዳቂ ሃዲሶችን (መውዱዕ) እንዲሁም ጠላቶች ስለሳቸው የቀጠፉትን ውሸት ማተላለፍ አይገባም።
ምክንያቱም ይህ ተግባር ከአመፀኞች ጎራ የሚያሰልፍ ስልሆነ ነው። የአላህ ምልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ
ያስጠነቅቁናል፡-
"من حدث عني حديثًا يرى أنه كذب فهو أحد الكذابين" رواه مسلم
“ሃሰት መሆኑን እያወቀ አንድን ሀዲስ ያስተላለፈ በርግጥ እሱ ከቀጣፊዎች አንዱነው። ” (ሙስሊም)
አንድ
ሙስሊም የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ንግግር ሲያስተላልፍ ሙሉ መልእክቱን ያለመቀነስ ያለምጨመር እንዲሁም
ትርጉሙንም ሆነ ሀሳቡን ሳይቀይርና ሳያዛባ ማስተላለፉን እርግጠኛ መሆን ይገባዋል። በዚህም የመልእክተኛው
(ሰ.ዐ.ወ) ዱዓ ይደርሰዋል። እንዲህ ይላሉ፡-
"نضر الله إمرءًا سمع منا حديثًا فبلغه، فرب مبلغ أحفظ من سامع" رواه ابن ماجة
“ አላህ ፊቱን ያብራለት ያ ንግግራችንን ሰምቶ በአግባቡ ላስተላለፈ ግለሰብ። ምናልባት አድማጭ ከአድራሽ የበለጠ ሊይዝ ይችላልና። ” (ኢብኑ ማጀህ)
11. እሳቸውን መርዳት
ይህ የሚሆነው አንድ ሙስሊም የሳቸውን ተግባርም ሆነ ንግግር በመከተል፣ ሱናቸውን ህያው በማድረግ እንዲሁም ኢስላምን በመርዳት ይሆናል። ጌታችንም እንዲህ ይለናል፡-
الَّذِينَ
يَتَّبِعُونَ الرَّسُولَ النَّبِيَّ الْأُمِّيَّ الَّذِي يَجِدُونَهُ
مَكْتُوبًا عِندَهُمْ فِي التَّوْرَاةِ وَالْإِنجِيلِ يَأْمُرُهُم
بِالْمَعْرُوفِ وَيَنْهَاهُمْ عَنِ الْمُنكَرِ وَيُحِلُّ لَهُمُ
الطَّيِّبَاتِ وَيُحَرِّمُ عَلَيْهِمُ الْخَبَائِثَ وَيَضَعُ عَنْهُمْ
إِصْرَهُمْ وَالْأَغْلَالَ الَّتِي كَانَتْ عَلَيْهِمْ فَالَّذِينَ آمَنُوا
بِهِ وَعَزَّرُوهُ وَنَصَرُوهُ وَاتَّبَعُوا النُّورَ الَّذِي أُنزِلَ
مَعَهُ أُولَٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ
ለእነዚያ
ያንን እነሱ ዘንድ በተውራትና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን የማይጽፍና የማያነብ ነቢይ የኾነውን መልክተኛ የሚከተሉ
ለኾኑት (በእርግጥ እጽፍለታለሁ)። በበጎ ሥራ ያዛቸዋል። ከክፉም ነገር ይከለክላቸዋል። መልካም ነገሮችንም ለነርሱ
ይፈቅድላቸዋል። መጥፎ ነገሮችንም በእነርሱ ላይ እርም ያደርግባቸዋል። ከእነሱም ላይ ሸክማቸውንና እነዚያንም
በእነርሱ ላይ የነበሩትን እንዛዝላዎች (ከባድ ሕግጋቶች) ያነሳላቸዋል። እነዚያም በእርሱ ያመኑ ያከበሩትም የረዱትም
ያንንም ከእርሱ ጋር የተወረደውን ብርሃን የተከተሉ እነዚያ እነሱ የሚያድኑ ናቸው። ( አል አዕራፍ 157)
12. አህለል በይትን (ቤተሰቦቻቸውን) ማክበርና መውደድ
የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የቤተሰባቸውን (አህለል በይትን) ጉዳይ በተመለከተ ትኩረት ሰጥተው አደራ ብለዋል። በአንድ የኹጥባ ንግራቸውም ላይ እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል፡-
" فأهل بيتي، أذكركم الله في أهل بيتي، أذكركم الله في أهل بيتي، أذكركم الله في أهل بيتي" رواه مسلم
“ ቤተሰቦቼን፤ የቤተሰቦቼን ነገር አደራ የቤተሰቦቼን ነገር አደራ የቤተሰቦቼን ነገር አደራ። ” (ሙስሊም)
ለመልእክተኞች ከተሰጡ ተአምራት በጥቂቱ
እወቅ! አላህ (ሱ.ወ) ለመልእክተኞች የተላኩበትን ማህበረሰብ የሚገዳደሩበት ልዩ የሆኑ ተአምራትን ይሰጣቸዋል። ይህም ለማስተባበያነት ምንም አይነት መረጃ ማምጣት እንዳይችሉ ለማድረግ ነው። እንደምሳሌ ለማንሳት፡- አላህ (ሱ.ወ) ነብዩላህ ሙሳ /ሙሴ/ (ዐ.ሰ)ን
ሲልካቸው ግብፅ ውስጥ በሚገኙት የፊርዓውን ህዝቦች መካከል ድግምት በእጅጉ የተስፋፋበት ወቅት ነበር። የፊርዐውን
ድግምተኞች ገመዶቻቸውንና ዱላዎቻቸውን በሰዎች አይን ላይ ድግምት በመስራት እባብ እንዲመስላቸው በማድረግ ያሻቸውን
ይሰሩ ነበር። ይህን የድግምት ተግባር የምታጋልጥ የነብዩላህ ሙሳን በትር አላህ በተአምርነት አመጣ። በትሯን ወደ እባብነት በመቀየርም የድግምተኞችን እባቦች እንድትውጥ ተደረገ። ለተመልካቹም በድግምትና በተአምር መካከል ያለውን ልዩነት በግልፅ ታየ።
የነቢዩላህ ዒሳንም /እየሱስ/ (ዓ.ሰ) ዘመን ብንመለከት የእስራኤል ልጆች በህክምና ጥበባቸው ጣራ የነኩበት ዘመን ነበር። አላህም (ሱ.ወ) ለነብዩላህ ዒሳ የሰጣቸው
አብዛኛው ተአምር ይህንን የህክምና ጥበብ ያማከለ ነበር። በአላህ ፈቃድ ለምጣሞችን ፈውሰዋል፣ ሲወለዱ አይነስውር
የነበሩ ሰዎችን አይናማ አድርገዋል፣ ሙታንን ቀስቅሰዋል። በርግጥ ሃኪሞች ከረጅም ጊዜ የህክምና ክትትልና ከተለየ
የመድሃኒት ቅመማ ጋር የለምጥ በሽታን ሊፈውሱ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን በመዳበስ ብቻ ሊያደርጉት አይችሉም።
ምናልባት ከጊዜ በኋላ አይኑ የጠፋን ሰው የአይኑን የማየት ጉልበት ሊመልሱለት ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ሲወለድ
አይነስውር የነበረን ሰው አይን መመለስ ግን በህክምናው አለም የማይቻል ነው። ሙታንን መቀስቀስም እንዲሁ። ታድያ
ነብዩላህ ዒሳም (ዐ.ሰ) በነዚህ በህክምናው አለም የማይቻሉ ተአምራትን ይዘው መምጣታቸው እሳቸው አንድ ተራ ሃኪም
እንዳልሆኑና ይልቁንም ከአለማቱ ጌታ የተላኩ ነብይ እንደሆኑ የማያወላዳ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል። ይህም ብቻ ሳይሆን
ከአወላለዳቸው ጀምሮ ብንመለከት የህክምናውን አለም ህጎች የጣሰና ተአምራዊ ነበር። ይህ ሁሉ ክስተት ህዝቦቻቸው
ይዘውት የመጡትን መልእክት ያለማንገራገር እንዲቀበሉ ምክንያት ነው ማለት ነው።
የአላህ
መልእክተኛ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሲላኩ ማንበብና መፀፍ የማይችሉ ነበሩ። ማንበብና መፃፍ ከሚችሉ ሰዎችም ጋር
የመሰብበሰብና የመቀማመጥ እድሉም አልነበራቸውም። ከመላካቸው በፊት በነበረው የህይወት ዘመናቸውም በተማሪነትም ሆነ
በመምህርነት አይታወቁም ነበር። በዘመናቸው እንደነበሩት ሰዎች የስነ- ፅሁፍ፣ የቅኔ እንዲሁም የግጥም ስራዎች
የሏቸውም። በየአደባባዩም ንግግር
አድርገው አያውቁም። በወቅቱ የአረበያ ምድር በባለቅኔዎች፣ በስነ- ፅሁፍ ሊቃውንት እንዲሁም በአንደበተ ርቱእ
ተናጋሪዎች የተሞላ ነበር። እሳቸው ግን ከነዚህ ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ አልነበሩም። ከመላካቸው በፊት ታድያ
ጌታችን አላህ ይህንን አረቦች የሚመፃደቁበትን የስን-ፅሁፍ ጥበብ የሚያስከነዳ፣ ከኔ በላይ ላሳር ያሉትን ሁሉ እጅ
የሚያሰጥ ድንቅ ተአምር ለመልእክተኛው ሰጣቸው። ታድያ እሳቸውም በንግግር አዋቂነታቸው በአረብያም ሆነ በተቀረው
አለም ተወዳዳሪ የሌላቸው ጥቅል ንግግር (ጀዋሚዕ አል ከሊም) በመናገር ብቸኛው ለመሆን በቁ። የተአምሮች ሁሉ
የበላይ፤ መላውን የሰው ልጅ የሚፈትን፤ ድንገት በአርባኛ አመታቸው ፈንጥቀው ለ 23 አመታት የዓረቦችን አፍ
አስከፍተው የቆዩበትን ድንቅ መልእክት ይዘው ብቅ አሉ። ቁርአንን። ይህ ተአምር ለመልእክተኝነታቸው በማያሻማ መልኩ
መረጃ ሆኖ መቅረብ ይችላል። ሌላ አጋዥ እንኳን ሳያስፈልገው። ምክንያቱም ይህንን ቁርአን መሰሉን እንዲያመጡ
ጠይቀዋቸው አልቻሉም፤ አስር ምእራፎችን ብቻ አምጡ አሏቸው አቃታቸው፤ እንደው አጭር የሆነቸውን ምእራፍ እንኳን
አምጡ አሉ አልተቻለም። በስተመጨረሻም የሰው ልጅ ሁሉ ቢሰበሰብ ከዚያም አጋንንትን በረዳትነት ቢጠሩና ሁሉም
ቢተባበሩ አንዲት አጭር ምእራፍ ማምጣት እንደማይችሉ አስረግጠው ነገሯቸው።
أَمْ
يَقُولُونَ افْتَرَاهُ قُلْ فَأْتُوا بِسُورَةٍ مِّثْلِهِ وَادْعُوا مَنِ
اسْتَطَعْتُم مِّن دُونِ اللَّهِ إِن كُنتُمْ صَادِقِينَ
በእውነትም «(ሙሐመድ) ቀጣጠፈው» ይላሉን?«ይህ ከሆነ መሰሉን (አንዲት) ሱራ አምጡ። ከአላህም ሌላ የቻላችሁትን ሁሉ (ረዳት) ጥሩ። እውነተኞች እንደሆናችሁ (ተጋግዛችሁ አምጡ)» በላቸው። (ዩኑስ 38)
ጌታችን አላህ
(ሱ.ወ) መልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) የሰው ልጅ ሊገነዘበው የሚችል ተአምር አጎናፀፏዋል። በርግጥ የንፁህ አእምሮ
ባለቤቶች ለነዚህ ተአምራት እጅ ይሰጣሉ። ያለማንገራገር ይቀበላሉም። በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ) በርካታ ቀልብን
የሚያረጋጉ ተአምራትን ለግሷቸዋል። በርግጥ ከነዚህ ተአምራት ፊቱን ያዞረ የጠፋ እንጂ ሌላ አይሆንም::