መቻልና ቁጣን መቆጣጠር (ክፍል 1)
የታጋሽነት ትርጉም
ቋንቋዊ ትርጉም፡- በቁጣ ወይም አንዳች መጥፎ ነገር በሚደርስ ጊዜ፡-
መበቀል እየቻሉ ረጋና ሰከን ማለት፡፡
እርጋታና ነፍስን መቆጣጠር፡፡
‹‹ሒልም›› የሚለው የዓረብኛ ቃል ‹‹አእምሮ›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ የሚከተለውን የቁርአን አንቀጽ ይመልከቱ፡፡
أَمْ تَأْمُرُهُمْ أَحْلَامُهُم بِهَٰذَا ۚ أَمْ هُمْ قَوْمٌ طَاغُونَ
“አእምሮዎቻቸው በዚህ ያዟቸዋልን? አይደለም በእውነቱ እነርሱ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦች ናቸው፡፡” (አል ጡር 32)
“ሐሊም” (ታጋሽ) ከአላህ መልካም ስሞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ኸጧቢ እንዲህ ብለዋል፡-
“አላህ በእርግጥም ይቅር ባይ፣ የማይቸኩል፣ ቁጣ የማያሸንፈው፣ የባለጌና የወንጀለኛ ድርጊት ወሰን የማያሳልፈው፣ ለቅጣት የማይቸኩል፣ ሁሉንም ነገር በወቅቱና በታቀደለት መጠን የሚፈጽም አምላክ ነው፡፡”
ገዛሊ እንዲህ ሲሉ አክለዋል፡-
“ቁጣ አሸንፎት ለብቀላ እንዲቸኩል የማያደርገው፡፡”
وَلَوْ
يُؤَاخِذُ اللَّهُ النَّاسَ بِمَا كَسَبُوا مَا تَرَكَ عَلَىٰ ظَهْرِهَا
مِن دَابَّةٍ وَلَٰكِن يُؤَخِّرُهُمْ إِلَىٰ أَجَلٍ مُّسَمًّى ۖ فَإِذَا جَاءَ أَجَلُهُمْ فَإِنَّ اللَّهَ كَانَ بِعِبَادِهِ بَصِيرًا
“አላህም
ሰዎችን በሠሩት ኀጢአት ቢይዝ ኖሮ በወለሏ (በምድር) ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ ባልተወ ነበር፡፡ ግን እተወሰነ ጊዜ
ድረስ ያቆያቸዋል፡፡ ጊዜያቸውም በመጣ ወቅት (በኀጢአታቸው ይቀጣቸዋል)፡፡ አላህ በባሮቹ (ኹኔታ) ተመልካች
ነውና፡፡” (ፋጢር 45)
ታጋሽነት የአእምሮን ምሉእነት እና ብርታት፣ እንዲሁም የቁጣ ጉልበት መሰበሩንና ለአእምሮ ፈቃድ ማደረን ያመለክታል፡፡
የታጋሽነት ጠቀሜታና ክብደት
1. ሰውየው መበቀል እየቻለ በመታገሱ እና ቁጣውን በመቆጣጠሩ መጠን ከአላህ ዘንድ ያለው ደረጃና ከፍ ይላል፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-
“መበቀል እየቻለ ቁጣውን የተቆጣጠረ አላህ በእለተ ቂያማ ከሰዎች መካከል ይጠራውና የፈለጋትን ሁረል አይን እንዲመርጥ ያደርገዋል፡፡” (ቲርሚዚና አቡ ዳውድ)
ኡባደት ቢን ሷሚት እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም፡-
“አላህ ግንብን ከፍ የሚያደርግበትን ነገር ልንገራችሁን?” “አዎ፣ ይንገሩን›› አሏቸው፡፡ ክፉ የሰራብህን መታገስህ፣ የበደለህን ይቅር ማለትህ፣ ለነፈገህ መስጠትህ፣ ዝምድናህን የቆረጠውን መቀጠልህ ነው” አሉ፡፡
ቁርአን እነዚህን ባህሪያት በመዘርዘር ለጀነት የሚያበቁ መሆናቸውን መስክራል፡፡
وَسَارِعُوا إِلَىٰ مَغْفِرَةٍ مِّن رَّبِّكُمْ وَجَنَّةٍ عَرْضُهَا السَّمَاوَاتُ وَالْأَرْضُ أُعِدَّتْ لِلْمُتَّقِينَ- الَّذِينَ يُنفِقُونَ فِي السَّرَّاءِ وَالضَّرَّاءِ وَالْكَاظِمِينَ الْغَيْظَ وَالْعَافِينَ عَنِ النَّاسِ ۗ وَاللَّهُ يُحِبُّ الْمُحْسِنِينَ
“ከጌታችሁ
ወደ ኾነችም ምሕረትና ስፋትዋ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ኾነች ገነት አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትኾን
ተቻኮሉ፡፡ ለእነዚያ በድሎትም ኾነ በችግር ለሚለግሱት፣ ቁጭትንም ገቺዎች ከሰዎችም ይቅርታ አድራጊዎች ለኾኑት
(ተደግሳለች)፡፡ አላህም በጎ ሠሪዎችን ይወዳል፡፡” (አሊ ዒምራን 133-134)
2. ታጋሽነትና ሆደሰፊነት የጠላትህን ጥላቻው በማሟሸሽ ወዳጅህ ያደርገዋል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-
وَلَا تَسْتَوِي الْحَسَنَةُ وَلَا السَّيِّئَةُ ۚ ادْفَعْ بِالَّتِي هِيَ أَحْسَنُ فَإِذَا الَّذِي بَيْنَكَ وَبَيْنَهُ عَدَاوَةٌ كَأَنَّهُ وَلِيٌّ حَمِيمٌ _وَمَا يُلَقَّاهَا إِلَّا الَّذِينَ صَبَرُوا وَمَا يُلَقَّاهَا إِلَّا ذُو حَظٍّ عَظِيمٍ
መልካሚቱና
ክፉይቱም (ጸባይ) አይተካከሉም፡፡ በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ጸባይ (መጥፎይቱን) ገፍትር፡፡ ያን ጊዜ ያ
ባንተና በእርሱ መካከል ጠብ ያለው ሰው እርሱ ልክ እንደ አዛኝ ዘመድ ይኾናል፡፡ (ይህችንም ጠባይ) እነዚያ
የታገሱት እንጅ ሌላው አያገኛትም፡፡ የትልቅም ዕድል ባለቤት እንጅ ማንም አይገጠማትም፡፡ (ፉሲለት 34-35)
ኢብን አባስ እንዲህ ብለዋል፡-
“አላህ ሙእሚኖችን ሲቆጡ እንዲታገሱ፣ ክፉ ሲሰራባቸው ሄደ ሰፊ እንዲሆኑ፣ የበደላቸውን ይቅር እንዲሉ አዟቸዋል፡፡ እነዚህን ካደረጉ አላህ ከሰይጣን ይጠብቃቸዋል፡፡ ጠላቶቻቸውንም ወዳጅ ያደርግላቸዋል'”[1]
ሆደ ሰፊነት የሰውየውን ውስጣዊ ጥንካሬና ክህሎት ያመለክታል፡፡ ኢብን መስዑድ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም፡-
“ከናንተ ዘንድ ብርቱ የምትሉት እንዴት ዓይነቱን ሰው ነው? ሲሉ ጠየቁ፡፡ “ሰዎች ታግለው የማያሸንፉት” የሚል ምላሽ ተሰጣቸው፡፡ “ግና ብርቱ ማለት በቁጣ ጊዜ ራሱን የሚቆጣጠር ነው፡፡” አሉ፡፡ (ሙስሊም)
አንድ ሰው ነቢዩን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም፡- “ይምከሩኝ፡፡ ግና እንዳልረሳው ምክር አያብዙብኝ” አላቸው፡፡ እርሳቸውም “አትቆጣ” አሉት፡፡ (ማሊክ)
4. ሰውየው ራሱን እንዳይስትም ያቅበዋል፡፡ አንድ ሰው ነፋስ ኩታውን ከላዩ ላይ ገፈፈችበት፡፡ በዚህ ተቆጥቶ ሲረግማት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሰሙ፡፡ “አትርገማት፡፡ ምክንያቱም በአላህ የታዘዘች ናት፡፡ እነሆ፣ ለእርግማን ተገቢ ያልሆነን አካል የረገመ እርግማኑ ወደርሱ ይመለሳል” አሉት፡፡ (ቲርሚዚ)
5. የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አንድ ቀን ምሽት ላይ ለሰዎች ንግግር አደረጉ፡፡ ከተናገሩት መሐል የሚከተለው ይገኝበታል፡-
“ሰዎች
ባህሪያቸው የሚበርድለት ሰው አለ፡፡ ቶሎ ተቆጥቶ ቶሎ የሚበርድም አለ፡፡ ሲቆጣም ሲበርድም በእርጋታ የሆነ አለ፡፡
የመጀመሪያው ሁለተኛውን ያካክስለታል፡፡ አዋጅ፣ ቶሎ ተቆጥቶ ቀስ ብሎ የሚበርድም አለ፡፡ ከሁሉም በላጬ ቀስ ብሎ
የሚቆጣውና ቶሎ የሚበርደው ነው፡፡ መጥፎው ደግሞ ቶሎ የሚቆጣውና ቀስ ብሎ የሚበርደው ነው፡፡ መጥፎው ደግሞ ቶሎ
የሚቆጣውና ቀስ ብሎ የማበርደው ነው፡፡ አዋጅ፣ ከሰዎች ውስጥ ሲያበድርም ሲበደርም መልካም የሆነ አለ፡፡ ሲያበድር
መጥፎ ሲበደር መልካም የሆነ አለ፡፡ ሲበደር መጥፎ ሲያበድር መልካም የሆነ አለ፡፡ የመጀመሪያው የሁለተኛውን
ያካክሰዋል፡፡ ሲያበድርም ሲበደርም መጥፎ አለ፡፡ አዋጅ፣ ከነዚህ ውስጥ በላጬ ሲያበድርም ሲበደርም መልካም የሆነው
ነው፡፡ መጥፎው ደግሞ ሲያበድርም ሲበደርም መጥፎ የሆነው ነው፡፡ አዋጅ፣ ቁጣ ከሰው ልጅ ልቦና ውስጥ ያለ ፍም
እሳት ነው፡፡ ሰው ሲቆጣ ዓይኖቹ እንዴት እንደሚቀሉና የደም ስሩ እንዴት እንደሚግተረተር አላያችሁምን? እንዲህ
ዓይነት ስሜት የተሰማው ሰው ወደ መሬት ይጠጋ፡፡ ባለበት ይቀመጥ፡፡” (ቲርሚዚ)
6.
ታጋሽነት የኢማንን ጥልቀት ያመለክታል፡፡ አንዳንዱ ሰው በቁጣ ጊዜ ዓቅሉን ይስታል፡፡ ያለማቋረጥ ይናገራል፣
ይበሳጫል፣ ፊቱ በጣም ይጨፈገጋል፡፡ ሲብስበት ወባ እንደያዘው ሰው ይንዘፈዘፋል፡፡ ይሳደባል፣ ይራገማል፣ ኢስላም
እንዲህ አይነቱን ባህሪ ይኮንናል፡፡
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-
“ሙእሚን ሰዎችን በምላሱ አይወጋም፡፡ ተራጋሚ፣ ተሳዳቢና ብልግና ተናጋረም አይደለም፡፡” (ቲርሚዚ)
[1] ሙኽተሰር ሚንሐጀል ቃሲዳን
[2] ኹሉቁል ሙስሊም (ገዛሊ)