የቁርኣን ታሪክ
ቁርአን
ንፁህ የሆነ የአላህ ቃል (ንግግር) ነው። በቁርአን ውስጥ የአላህ ቃል ያልሆነ ነገር የለበትም። ቁርአን
የኦርጅናል ባህርይውን እንደያዘም ዛሬን ሊደርስ ችሏል። ወደ ሰነድነት ሲቀየርም በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የበላይ
ተቆጣጣሪ አማካኝነትነት ነው። እያንዳንዱ ምዕራፍ የት መቀመጥ እንዳለበት ለፀሀፊዎቻቸው ትዕዛዝ ይሰጡ ነበር።
በዚህም ሁሉም የቁርአን ምዕራፎች በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ትዕዛዝ ተደርድረው የተቀመጡ ናቸው።
በረሱል የህይወት ዘመን የቁርአን መጠበቂያ ዘዴዎች
ከሰሓቦች መካከል የፅህፈት ክሂል የነበራቸው የቁርአንን ብዙውን ክፍል መዝግበው ቆይተዋል። በዚህ ሁኔታም ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በህይወት በቆዩበት ዘመን ቁርአን በአራት መንገዶች ጥብቅ ሆኖ ሊቆይ ችሏል።
- ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሁሉም የቁርአነ አንቀፆች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያሉት ተመዝግበው እንዲቆዩ አድርገዋል
- ብዙዎቹ ሰሓቦች የቁርአንን ጠቅላላ አንቀፆች በአዕምሯቸው (በልባቸው) ይዘዋል።
- ሶላት ካለቁርአን ስለማይሰገድ፣ ሁሉም ሶሓቦች ማንም ሳይቀር ከቁርአን የተወሰነውን በአዕምሯቸው ይዘዋል። በረሱል የመሰናበቻ ሐጅ ሥርዓት ወቅት ቁጥራቸው አንድ መቶ አርባ ሺ የሚሆኑ ሶሓቦች መገኘታቸው የሶሓባዎችን ብዛት ያመላክተናል።
- ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል የፅህፈት ክሂል ያላቸው ሶሓቦች ቁርኣንን መዝግበው የያዙበት የየራሳቸው ሰነድ በየግላቸው ነበራቸው። ይህንንም ለራሳቸው ይጠቀሙበት ነበር። በያዙትም ሰነድ እርግጠኛ ለመሆምን እረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ያረጋገረጡ ነበር።
ከረሱል ህልፈት በኋላ የቁርአን ጥበቃ
አሁን
ያለው ቁርአን ቃል በቃል ያኔ በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ላይ የወረደው መሆኑ የማይካድ ታሪካዊ እውነታ ነው። አቡበክር
ከነብዩ ህልፈት በኋላ ቁርአን በአዕምሮቸው (በልባቸው) ያሳድሩ (ሁፋዝ)ንና ቁርአን በተለያዩ ነገሮች መዝግበው
የያዙ ሰነዶች (ቆዳ፤ አጥንት፤ ወዘተ)ን በአንድ መፅሀፍ ይሰናዳ ዘንድ ሰበሰቡ። በኸሊፋው ዑስማን ጊዜ ደግሞ
የኦርጅናል ኮፒዎች ወደ ተለያዩ ኢስላማዊ ከተሞች ተሰራጩ። የእነዚህ ኦርጂናል ኮፒዎች ዛሬ ዓለም ላይ ይገኛሉ።
ለምሳሌ አንደኛው ኦሪጂናል ኮፒ ኢስታንቡል ሲገኝ ሌላኛው ደግሞ ታሽከንት ውስት ይገኛል። እነዚህ ኮፒዎች ማንኛውም
ሰው አሁን በዓለም ካሉት የቁርአን ቅጂዎች ጋር ቢያመሳክር ምንም ልዩነት አያገኝበትም።
እንዴት
በቁርአኖቹ ሰነዶች ላይ የይዘት መጣረስ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል? በዓለማችን ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ በየትውልዱ
በሚሊዩን የሚቆጠሩ ቁርአን በልባቸው የያዙ ሙስሊሞች እያሉ? አንድን የቁርኣን ፊደል ለመቀየር ቢሞከር እኝህ
በሚሊዮን የሚቆጠሩት ሁፋዞች ወዲያውኑ ያጋልጡታል።
ባለፈው ክ/ዘመን (20 ኛው) ጀርመን የሚገኘው የሙኒኽ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ ኢስላማዊ ሀገሮች ውስጥ በእያንዳንዱ ዘመን ላይ የነበሩ በተለያዩ ቁሶች ላይ የተፃፉ 42000 (አርባ ሁለት ሺ) የቁርአን ቅጂዎችን ሰብስቧል። ማለትም መረጃዎቹ የተሰበሰቡበት ከመጀመሪያው ሂጅራ ጀምሮ እስከ 14ኛው ዘመን ሂጅራ ድረስ ያሉትን መረጃዎች ከተለያዩ የአለማት ክፍል ያካተተ ነበር። ዩኒቨርስቲውም በእነዚህ የቁርአን ቅጂዎች ላይ ለ50
(ግማሽ ክ/ዘመን) አመታት ያህል ጥናት አደረገ። በጥናቱም መሰረት አንዳንድ የኮፒ አደራረግ ስህተት በስተቀር በ
አርባ ሁለት ሺዎቹ የቁርአን ቅጂዎች መካከል ምንም አይነት ልዩነት እንደሌለ አረጋገጠ። ይህ የዩኒቨርሲቲው አካል
የሆነው ተቋም በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ቢወድምም የጥናቱ ውጤት ግን ሊተርፍ ችሏል።
ሌላው
ወሳኝ ጉዳይ ደግሞ ቁርአን ከሰማይ ወደ ምድር ሲመጣበት (ሲተላለፍበት) የነበረው የአረብኛ ቋንቋ አሁንም
በዘመናችን በሰፊው ግልጋሎት እየሰጠ ያለ መሆኑ ነው። አሁን ይህ ቋንቋ ከሞሮኮ እስከ ኢራቅ ላሉ ሶስት መቶ ሚሊዩን
ለሚቆጠሩ ዐረቦች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዐረብ ያልሆኑ ሰዎችም በየሃገሩ ቋንቋውን
ይማሩታል፣ ያስተምሩታል።
ጥንታዊ የሆነው የዓረብኛ ቋንቋ ሰዋሰው (ነሕው)እና ስነ-አገባብ (ሶርፍ) እንደ ጥንቱ ዛሬም ሳይቀየር የቋንቋው አካል ሆነው ይገኛሉ። ዛሬ ዘመናዊ አረብኛ የሚናገር ሰው በቀላሉ ከዛሬ 1400
አመታች በፊት የነበረውን ቁርአን መረዳት ይችላል። ይህ አይነቱ ልዩ ባህሪይ ለረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እንጅ ለሌሎቹ
ነቢያት የታደለ ጉዳይ አይደለም! ለዓለም መድህን የመጣው ቁርአን ጥንትም እንደነበረው ዛሬም በዛው ገፅታው ላይ
ይገኛል፤ ወደፊትም በዚሁ መልክ ተጠብቆ ይቆያል።
إِنَّا نَحْنُ نَزَّلْنَا الذِّكْرَ وَإِنَّا لَهُ لَحَافِظُونَ [١٥:٩]
“እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው። እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን።” (አል-ሂጅር 15፤9)