ወንድማማችነት እና ሚስባሃ
አንድ
ዳዒ “ወንድማማችነት እና ለአላህ ብሎ መዋደድ ለሙስሊሞች እጅግ አስፈላጊ ስለመሆኑ” በሚለው ርእስ ዙሪያ የሙሃደራ
ፕሮግራም ነበረው። የሙሃደራ ቀኑ ከመድረሱ በፊትም ስለ ሙሃደራው ይዘትና አቀራረብ ማስተንተን ያዘ። ከዚህ ቀደም
በሚያቀርበው መልኩ በርዕሱ ዙሪያ የወረዱ የቁርዓን አንቀፆችንና ሀዲሦችን በማሰባሰብ ከአንዳንድ ታሪኮችና የሠለፍ
ምሳሌዎች ጋር በማዋሃድ ያቅርብ ወይንስ ሌላ መንገድ ይከተል… ከራሱ ጋር ሀሣብ ያዘ።
በመጨረሻም
ከዚህ ቀደም ያቀርብ በነበረው መልኩ የማቅረብ ሀሣቡን ሠረዘ። ለምን ቢባል ፕሮግራሙ ላይ የሚታደሙ ሰዎች
የቁርዓኑንም ሆነ የሀዲሱን መረጃዎች ጠንቅቀው የሚያውቁና በተደጋጋሚም የሠሙ ናቸው። ይህ ከመሆኑ ጋር ግን
የወንድማማችነት ግንኙነታቸው አሁንም እጅግ ደካማ ነው። የተሠላቹና የተራራቁም ናቸው።
ስለሆነም
ዳዒው አዲሱ አቀራረቡ ምን መምሰል እንዳለበት ማሰብ ያዘ። አላህ (ሱ.ወ) ወደ ሀሳቡ ይመራውም ዘንድ በሱ ታገዘ።
በመጨረሻም አንድ ሀሳብ መጣለት። ሀሳቡን ለማንም ሣይናገር በውስጡ በመያዝ ለፕሮግራሙ የሚያስፈልጉትን ነገሮች
አዘጋጀ። በቀጠሮው ቀንም ወደ ሙሃደራ ቦታው ሄደ...
ዳዒው
በተዘጋጀለት ቦታ ላይ ተደላድሎ ተቀመጠ። ንግግሩንም አላህን በማወደስና በማሞገስ በመልእክተኛውም (ሰ.ዐ.ወ) ላይ
ሰለዋት በማውረድ ጀመረ። ከዚያም ከኪሱ አንድ ረጅም ሚስባሃ (ዚክር መቁጠሪያ) አወጣ። ለታዳሚዎቹም በማሣየት ስሟ
ምን እንደሆነ ጠየቀ። እነርሱም “ሚስባሃ” በማለት በአንድ ድምፅ መለሱለት። በደንብና በጥንቃቄ እንዲመለከቷት ወደ
ግራ ወደ ቀኝ በማዟዟር አሣያቸው።
ለተወሰነ
ጊዜ ዝም ብሎ ከቆየ በኋላ ከኪሱ መቀስ በማውጣት የሚስባሃዎቹን ፍሬዎች የሚያይዘውን ክር መሃል ላይ ቆረጠ።
ፍሬዎቹ በመፈናጠር እዚህም እዚያም ተበታተኑ። ታዳሚዎች እየሆነ ያለውን በማየት በግርምትና በተደናገጠ ሁኔታ
ተመለከቱ።
በዚህን
ጊዜ ዳዒው ዝምታውን በመስበር እንዲህ አላቸው። “ከአላህ ጋር ከሚያስተሳስረው ጠንካራ ግንኙነት ኢማን ቀጥሎ ለዚህ
ኡምማ ዋስትና የሚሆነው የወንድማማችነት ትስስር ነው። ወንድማማችነት በእስልምና ጥሪ ሥር የተሠባሰቡ ልጆችን ቀልብ
የሚያስተሳስርና የሚያያይዝ ገመድ ነው። ይህ ገመድ የደከመ አሊያም የተበጠሠ እንደሆነ ልቦች ይበታተናሉ፤
ይራራቃሉ፤ ይጠፋፋሉ። ይህም መልእክቱን ለማዳረስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ አለው።”
አለ - ዳዒው።
በቦታው
ላይ ዝምታ ነገሠ። ታዳሚዎቹም ከዳዒው ማብራሪያ በመነሳት የሁኔታውን አደገኛነት አስተዋሉ። መልእክቱም በትክክል
ገባቸው። ሚስባሃዋን መልሰው በጠንካራ ገመድ እንደገና ለማያያዝም የተበታተኑትን ፍሬዎች ከየቦታው መልቀም ያዙ።
ቀጥሎም እርስ በርሣቸው በውዴታና በፍቅር ወደ መተቃቀፍ ገቡ። ዐይናቸው እንባ አቅሯል፤ ልባቸው በፍርሃት ርዷል፤
ደረታቸው ለወንድማቸው ለስልሷል፤ ውስጣቸው ንፁህ ሆኗል። በዚህ ኢማናዊ ድባብ ውስጥ ባሉበት ሁኔታ አንድ እንዲህ
የሚል ድምፅ ሲደጋገም ሰሙ።
وَالَّذِينَ كَفَرُوا بَعْضُهُمْ أَوْلِيَاءُ بَعْضٍ إِلَّا تَفْعَلُوهُ تَكُن فِتْنَةٌ فِي الْأَرْضِ وَفَسَادٌ كَبِيرٌ [٨:٧٣]
“እነዚያም የካዱት ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው። (ከምእምናን መረዳዳትን) ባትሠሩት በምድር ላይ ሁከትና ታላቅ ጥፋት ይኾናል።” (አል-አንፋል 8፤ 73)
በዚህን
ጊዜ ቶሎ በመሽቀዳደምም “ምንም አይከለክለንም። እናደርጋለን.. እንሠራለን… እናደርጋለን..” አሉ። በእውነተኛ
የመነሣሣት ስሜት ውስጥ በገቡበት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሌላ የአንድ ጠያቂ ድምፅ ሰሙ።
“ለምንድነው
ወንድማማችነታችንና ግንኙነታችን ሊዳከም የቻለው? ከዚህ በፊት አሁን ካለንበት ሁኔታ በተሻለ መልኩ አልነበርንም
ወይ?.. ከዚህ ቀደም ኢስላማዊ የወንድማማችነት ግዴታችንን በሚገባ እንወጣ ነበር። እንዘያየር፣ ስጦታ እንሠጣጥ፣
አንደኛችን ሲጠፋ እንጠያየቅ ነበር። እያንዳንዳችን ለወንድማችን ልዩ ክብር ነበረን። ሲልከን እንላከዋለን፣
ሲያማክረን እናማክረዋለን፣ ሲጠራን አቤት እንለዋለን፣ በሌለበት አጠቃላይ ሁኔታውን እንጠይቃለን፤ ሃጃውን
ሣንፈፅምለት ፈፅሞ እንቅልፍ አይወስደንም፤ ሀሳቡን ሣናሣካለት ሀሳባችን አያርፍም፤ አላህ ሁሉንም ነገር
እስኪያገራለት ድረስ አብረነው እንሆን ነበር። ታዲያ አሁን ምን ነካን!!”
አሁንም
ዝምታው ሠፈነ። ሁሉም በቀደሙ ትዝታዎቹ ውስጥ ተሳፈረ። የድሮውን ጀመዓ ፍቅርና መተሣሰብ አሠበ። ያንን ትሩፋቱ
ዛሬም ድረስ የሚያውድ መልካምና ቆንጆ ጊዜ አስታወሠ። አስከትለውም በቁጭት ጠየቁ። ወንድማማችነታችን በፊት
እንደነበረው መልኩ ለመመለስ ለምንድነው ያቃተን? ምንድነው ምክኒያቱ? አሉ። የተለያዩ ምክኒያቶችና ሀሳቦች
ተሠነዘሩ። የኑሮ ሁኔታው፣ የጊዜ ጥበቱና የሥራ ብዛቱ .. ከቀረቡት ምክኒያቶች ከፊሎቹ ነበሩ።
እውነተኛው ምክኒያት
ሙሃደራውን
ያቀረበው ዳዒ የሁሉንም ሀሳብና አስተያየት ካዳመጠ በኋላ “በርግጥ ይህ የምትሉት ምክኒያት እውነተኛውና ትክክለኛው
ከሆነ በፊት ወደነበርንበት የወንድማማችነት መንፈስ ለመመለስም ሆነ አሁን በአዲስ መልኩ ወንድማማችነታችንን ጠንከር
ባለ መልኩ ለማስኬድ ምንም ተስፋ አይኖረንም ማለት ነው። ሚስባሀውም በቅርብ ይሁን በሩቅ ጊዜ ውስጥ የመበጠሷ
ነገር እርግጥ ነው። ነገርግን ወደ አላህ ኪታብ /ቁርዓን/ እና ሱናው /ሀዲስ/ የተመለስን እንደሆነ ግን
ወንድማማችነት በአስተማማኝ መልኩ ተያይዞ ያለው በሱ መሆኑን እንረዳለን። ሁላችሁም አልጠቀሣችሁትም እንጂ የዚህ ሁሉ
መዳከም መንስኤው ኢማን ነው። አላህ (ሱ.ው) እንዲህ አለ
إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ إِخْوَةٌ [٤٩:١٠]
“ምእመናኖች ወንድማማቾች ናቸው።” (አል-ሁጁራት 49፤ 10)
በሌላ የቁርዓን አንቀፅ ደግሞ
وَالْمُؤْمِنُونَ وَالْمُؤْمِنَاتُ بَعْضُهُمْ أَوْلِيَاءُ بَعْضٍ [٩:٧١]
“ምእምንና ምእምናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው።” (አት-ተውባ 9፤ 71) ብሏል።
ስለሆነም
ሁላችንም እስቲ እናስታውስ። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በስደት መዲና እንደደረሱ መጀመሪያው የሰሩት ነገር
የእምነት ምልክት የሆነውን መስጊድን ነው። ቀጥለው ደግሞ በአንሷሮችና ሙሃጅሮች መካከል ወንድማማችነትን እንዲፈጠር
አደረጉ። ኡኹዋህ /ወንድማማችነት/ ከኢማን ጋር የተሣሠረ ነው። ከፍሬዎቹም አንዱ ነው። ኢማን ከፍ ያለ እንደሆን
የወንድማማችነት ደረጃውም ከፍ ይላል። ኢማን የወረደ እንደሆነም ይወርዳል። ኢማን በመታዘዝ እንደሚጨምር ባለመታዘዝ
እንደሚቀንሰው ሁሉ ኡኹዋህ /ወንድማማችነትም/ እንዲሁ እሱን ለማጠናከር መደረግ ያለበት ነገር ከተደረገ ከፍ
ካልተደረገና ችላ ከተባለ ደግሞ ዝቅ ማለቱ አይቀርም። መፍትሄው እንግዲያውስ በውስጣችን ደፍርሦና ዘቅጦ ያለውን
ኢማን በማነቃቃት ሥራ ላይ ማዋል ነው። ኢማን ሲነቃቃ የወንድማማችነት መንፈሱም አብሮ ይነቃቃል። ያድጋል ይፋፋል።”
የሙሃደራው
ታዳሚዎች በሀሣቡ መስማማታቸውን እራሣቸውን በመነቅነቅ ገለፁ። እንዲህም የሚሉ ይመስላሉ “በኢማናችን መዳከም
የተዳከመው ወንድማማችነታችን ብቻ አይደለም። በመካከላችን በግልፅ የሚታዩ በርካታ ነገሮች አሉ። በመሆኑም ኢማናችን
ወደ ማደሱና ማነቃቃቱ እርምጃ ካልፈጠንን ይህ ነገር ሥር የሠደደ በሽታ ይሆንና ለማከምም ሆነ ለማዳን አስቸጋሪ
እንዳይሆን ያሠጋል።”